ነሐሴ 23 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ህንድ እና ካናዳ ለ10 ወራት ያህል ተቋርጦ የቆየውን ከፍተኛ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማደስ የሚያስችላቸውን አዲስ መልዕክተኞች መሾማቸውን አስታውቀዋል። ይህ እርምጃ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ እንደ ትልቅ ምዕራፍ እየታየ ነው ተብሏል።
ህንድ፣ የአሁኑን በስፔን የነበራት አምባሳደር የሆኑትን ዲኔሽ ኬ. ፓትናይክን ወደ ካናዳ አዲስ ከፍተኛ መልዕክተኛ አድርጋ ስትሾም፣ ካናዳ በበኩሏ ልምድ ያላቸውን ዲፕሎማት ክሪስቶፈር ኩተርን ወደ ኒው ዴልሂ መላኳን ይፋ አድርጋለች።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከ2023 ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻክሮ ነበር። የችግሩ መንስኤም የካናዳ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ የሲክ ተገንጣይ መሪ ሃርዲፕ ሲንግ ኒጃር ግድያ ላይ የህንድ መንግስት እጅ አለበት የሚል ክስ ማቅረባቸው ነበር። ህንድ በበኩሏ ይህንን ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጋዋለች። በወቅቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማቶችን የማባረር ሂደትም ተካሂዶ ነበር ተብሏል።
አሁን ላይ ግንኙነቱ እንዲሻሻል መንገድ የተከፈተው፣ የካናዳ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር በቅርቡ ባደረጉት ውይይት ነው። በውይይታቸው ወቅት፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ መስማማታቸው ተዘግቧል።
ይህ አዲስ የዲፕሎማቲክ ሹመት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የጠፋውን እምነት ለመገንባት እና በንግድ፣ በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች ትብብራቸውን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ ይጠበቃል። ካናዳ በህንድ ውስጥ የቪዛ አገልግሎቶችን ወደነበረበት የመመለስ ፍላጎት ያላት ሲሆን፣ ህንድ ደግሞ በካናዳ የሚኖሩ የራሷን ዜጎች ደህንነት በተመለከተ ያላትን ስጋት እንድትፈታ ትፈልጋለች ነው የተባለው።
ምላሽ ይስጡ