በሃገራችን የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት አዋጅ ቢኖርም አሁንም የሚታየው የስራ ስምሪት የአካል ጉዳተኛ ሰራተኛውን ያማከለ አሰራር ባለመኖሩ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት እየተሰራ መሆኑን ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ናቸው ።
ፌዴሬሽኑ በትኩረት እየሰራ ከሚገኝባቸዉ ጉዳዮች አንዱ አዋጁ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ አመራሮችን ጨምሮ የሰው ሃብት አስተዳደሮችንና የሲቪል ማህበራትን የማሰልጠንና ግንዛቤን የማጎልበት ስራ ተጠቃሽ ነዉ፡፡
አሁንም በስልጣን ላይ ያሉና በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ የተገኙ ከ 20 ያላነሱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት አመራሮች ስለ አዋጁ ግንዛቤ ያላቸው ሁለቱ ብቻ መሆናቸውንና የተቀሩት ስለአዋጁ መኖር ጭርሶም እንደማያውቁ ገልጸዋል ።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ እየተደረጉ ያሉ የቅጥር ሂደቶች አካል ጉዳተኛውን ያካተተና ተቀጣሪው ያለበትን የጉዳት መጠን ያማከለ አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት በአስተዳደር ደረጃ ግንዛቤ ክፍተት እንዲሰፋ ማድረጉን ሃላፊዉ ጠቁመዋል፡፡
ይህ አዋጅ ተፈጻሚ እንዲሆን እና አካታችነት በተቋማት እንዲተገበር የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባና አሁን ላይ የተማሩና ስራ አጥ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አሰራር ሊኖር እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት አዋጅ ተፈጻሚ እንዲሆን ብሎም አካል ጉዳተኛውን ያማከለ ወጥ የሆነ የቅጥር ስርዓት እንዲፈጸም የመከታተል ስራን እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ